መገለል እና ፍረጃ የጋረደው ድንቅ ፈጠራ ችሎታ

Blog post description.

7/11/20251 min read

መገለል እና ፍረጃ የጋረደው ድንቅ ፈጠራ ችሎታ (እውነተኛ ታሪክ)።

በልጅነት ዕድሜ ላይ እያለሁወፈፌው ሹጌበመባል የሚታወቅ አንድ ወጣት በመንደራችን ውስጥ ይኖር ነበር።ወፈፌው ሹጌ” የሚለው ስም የቁልምጫ ስም አልነበረም; ይልቁንም ስያሜው በጊዜው ማህበረሰቡ የነበረውን የግንዛቤ ማነስ ማሳያ ነበር። በማህበረሰባችን ውስጥ ስለ ኦቲዝም የሰማ ወይም ብዝሃ አዕምሮን የተረዳ ሰው አልነበረም። ይልቁንም ከጠባብ ግምታችን እና አስተሳሰባችን ጋር የማይስማሙትን ላለመቀበል፣ለማግለል እና ለመፈረጅ እንደ ምክያት ተጠቅመንበታል። እኔም በልጅነት አዕምሮዬ ስለ ሹጌ የማውቀው ከሰፈር ሰው የሰማሁትን “ወፈፌነቱን” እንጂ በውስጡ የነበርውን ድንቅ ክህሎት አልነበረም። የሹጌን ደንቅ የተፈጥሮ ችሎታ የጊዜው የአግላይነት ባህል ጋርዶት ነበር። ዛሬ ላይ ቆሜ ሹጌን ሳስታውሰው ምንም እንኳን መገለል ቢኖርበትም፣ ልዩ ችሎታውን ተጠቅሞ የእለት ችግሩን ከመፍታት ወደኋላ አላለም ነበር። አብዛኛው የመንደሩ ሰው በባዶ እግሩ በሚሄድበት ዘመን ሹጌ የወዳደቁ ጎማዎችን ተጠቅሞ ጫማ ለራሱ በመስራት እኔ “ወፈፌ” አይደለሁም ይለን ነበር። በሌላው ዓለም ዲና የሚባለውን የሌሊት ለብስ በሰፈሩ በማይታወቅበት ዘመን ሽጌ የተላያዩ ቀለማት ያላቸውን እላቂ ቁርጥራጭ ጨረቆች ተጠቅሞ የራሱን ዲና በመስፋት ብሩህ ችግር ፈቺ አዕምሮ እንዳላው ሊያሳየን ሞክሮ ነበር። ዳሩ ግን ይህን ችሎታ መገለል እና ፍረጃ ሽፍኖት ስለነበር መቀበል አልቻልንም። ይህን ድንቅ ስራ ተገንዝበን ማበረታታት አለመቻላችን፣ ፈጠራ፣ ብልህነት እና በራስ መተማመን ምን እንደሆነ ለይተን ለማወቅ ተስኖን እንደነበር ዛሬ ላይ ቆሜ መናገር እችላለሁ።

ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስበው ህብረተሰቡ እንዴት ሹጌን እንዳገለለው እና እንደፈረጀው በቻ ሳይሆን የምረዳው ተሰጥዖውን ለማዳበር አለመሞከራችን እና ችላ ማላታችንንም ጭምር ነው። ሹጌ ከሚኖርበት ማህበረሰብ ወጣ ያለ ማንነት ቢኖረውም ያለውን ተፈጥሮዊ ችሎታ ተጠቅሞ የራሱን ችግር ከአብዛኛው ማህበረሰብ በተሻለ መልኩ መፍታት የቻለ ነበር። ስለ ኦቲዝም እና ተጓዳኝ የአዕምሮ እድገት ልዪነት ግንዛቤ እና እውቅት በሌለበት ዘመን እንደ ሹጌ ያሉ ብዙ የአለማችን ልጆች፤ በኖሩበት ማህበረሰብ እውቅና ስለተነፈጉ እና ስለተገለሉ ድንቅ ችሎታቸውን ሳንጠቀምበት ይህን አለም ተሰናብተዋል። ይህ አስተሳሰብ በብዙ የአለማችን አገሮች እየተቀየረ ቢሆንም በአሁጉራችን አፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ልዩ ፍላጎት ስላላቸው ህጻናት ያለንን አሉታዊ አመለካከትን ለመቀየር እና ለልጆቹ አስቻይ ምህዳርን ለመፍጠር ብዙ ሰራን ይጠይቃል። ብዝዎቻችን ስለ ኦቲዝም እና ሌሎች ተጓዳኝ የአዕምሮ ውስንንት ያለን ግንዛቤ በሹጌ ዘመን ክነበረው አስተሳስብ ብዙ የራቀ አይደለም። የዚህ ጽሑፍ አላማ የሹጌን አሳዛኝ ታሪክ ለመተረክ ሳይሆን ዛሬም እንደ ሹጌ በመገለል እና በመፈረጅ ደንቅ ተሰጥዖቸው ተጋርዶ ላለ ህጻናት አመቺ እና አካታች ምህዳር ለመፍጠር የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ነው።

ኦቲዝም እና ሌሎች የአዕምሮ እድገት ልዩነቶችን ለማስተናገድ በአካታች ትምህርት እና ግንዛቤ ላይ ስንሰራ፣ የሹጌ ትውስታ ወሳኝ መልእክት አለው። ሹጌ እኛ የምንጠብቀው ማህበራዊ ክህሎት ባይኖረውም የራሱ የሆነ ልዩ ተሰጥዖ ነበረው። ይሁን እንጂ የአካታችነት እና የቅቡልነት ባህል በማህበረሰቡ መካካል ስላላደገ የሹጌን ችግር ፈቺ ክህሎትን በመገለል ግርዶሽ ምክንያት ልናሳድገው እና ልናዳብረው አልቻልንም። ዛሬም የሹጌ እጣፋንታ የደረሰባቸው በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ህጻናት በኢትዮጵያ ይገኛሉ። የእነዚህ ህጻናትን እና የወላጆቻቸውን የነገ ተስፋ ለማስቀጠል አስቻይ፤አካታች እና አሳታፊ የፖሊሲ እና የህግ ማዕቀፍ ያስፈልጋል። እነዚህ ማእቀፎች አስቻይ ምህዳር ለመፍጠር ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። አስቻይ ምህዳር መፍጠር ከተቻለ ደግሞ፡

· ልዪፍላጎትን ያካተተ ስርዐተ ትምህርት መቅረጽ ይቻላል።

· የሰው ኃይልን ማሰልጥን አስቸጋሪ አይሆንም።

· አካታች የትምህርት ስርዓት ለመተግበር መልካም እድልን ይፈጥራል

· የአካታች ትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን ለማዘጋጀት እና ለማደራጀት ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል።

ማጠቃለያ፡ የዚህ ድህረ-ገጽ አላማ በአካታች ትምህርት ፖሊሲ፣ በስርዐተ ትምህርት ዝግጅት፣ በሰው ኃይል ስልጠና እና ማህበራዊ ግንዛቤ ዙሪያ በኢትዮጵያ ብሎም በአፍሪካ ደረጃ ተጨባጭ ለውጥ ላማምጣት በእውቀት፤ በሙያ እና በመስኩ የካበተ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎች አማካይነት እገዛ ማድረግ ነው። አላማችንን እና ስራችንን በበለጠ ለመረዳት በድህረ-ገጻችን ላይ በተቀመጠው አድራሻ ሊያገኙን ይችላሉ።